1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዜና | 11.02.2012 | 15:46

የሱዳን-ሱዳን ያለመጠቃቃት ውል

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በአፍሪቃ ሕብረት አማካይነት አዲስ አበባ ላይ ባካሄዱት ድርድር እርስበርስ ያለመጠቃቃት ውል ተፈራረሙ። ውሉን የተፈራረሙት የሰሜናዊው ሱዳን የጸጥታ ሃላፊ ሞሐመድ አታና የደቡብ ሱዳኑ የሥልጣን አቻቸው ቶማስ ዱዝ ናቸው። ሁለቱ ወገኖች በስምምነቱ አንዱ የሌላውን ወገን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ ነጻነት ለማክበር፤ እንዲሁም ከማንኛውም ጥቃት ለመቆጠብ ቃል ገብተዋል። ውሉን ያፈራረሙት የአፍሪቃ ሕብረት ዋና አማካይና የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ታቦ እምቤኪ ናቸው። ሁለቱ የሱዳን መንግሥታት በርካታ የድንበር ውዝግቦች ሲኖሯቸው እነዚሁ ወደፊት በአንድ የጋራ ኮሚሢዮን እንዲፈቱ ይደረጋል። ደቡብ ሱዳን ባለፈው ሐምሌ ወር ነጻነቷን ካወጀች ወዲህ ሁለቱ ግዛቶች በነዳጅ ዘይት ክፍፍል ጉዳይም ሲወዛገቡ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው። በደቡብ ሱዳን ይዞታ ስር የሚገኘው ነዳጅ ዘይት ከጠቅላላው ሶሥት-አራተኛ ይሆናል። 

አዲስ የሶሪያ ውሣኔ ረቂቅ

የሶሪያን ዓመጽ ለመግታት በቅርቡ ለጸጥታው ም/ቤት ቀርቦ የነበረው የውሣኔ ድምጽ አሰጣጥ ከከሸፈ ወዲህ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ በሳውዲት አረቢያ ጥያቄ በጉዳዩ እንደሚያተኩር ተነገረ። የአሜሪካው ቴሌቪዥን ጣቢያ CNN እንደዘገበው በሳውዲው አመራር ትናንት የተሰራጨው የአረብ ሊጋን የስላም ዕቅድ የሚደግፍ ረቂቅ የሶሪያን መንግሥት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ድርጊትም በጥብቅ የሚኮንን ነው። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሜሣር ናቪ ፒላይ በፊታችን ሰኞ ሶሪያ የምትገኝበትን ሁኔታ ለድርጅቱ ጠቅላይ ጉባዔ ያብራራሉ። ይህ በዚህ እንዳለ በፕሬዚደንት ባሽር-አል-አሣድ ድጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል በተካሄደ አዲስ ውጊያ በዛሬው ዕለት 28 ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል። ከነዚሁም ሃያ የሚሆኑት የሞቱት ተቃውሞው ጠንክሮ በሚካሄድባት ከተማ በሆምስ ነው።   

ኢራንና አከራካሪው የአቶም መርህ

የኢራኑ ፕሬዚደንት ማሕሙድ አሕማዲኔጃድ አገራቸው የዋሺንግተንና የአውሮፓ ሕብረት ጠናካራ ግፊት ሳይበግራት ስሞኑን አዲስ የአቶም ፕሮዤ እንደምታስተዋውቅ ገለጹ። አሕማዲኔጃድ ዓለም በሚቀጥሉት ቀናት ኢራን አዲስ የአቶም ጣቢያ ስትከፍት ይታዘባል ሲሉ ተናግረዋል። ፕሬዚደንቱ ይህን የተናገሩት ቴህራን ውስጥ የኢራኑ እሥላማዊ ዓብዮት 33ኛ ዓመት በተከበረበት የአደባባይ ስነ ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር ነው። አሕማዲኔጃድ ይሁንና የፕሮዤውን ይዘት በዝርዝር አላብራሩም። አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ማዕቀባቸውን ይበልጥ በማጠናከር የኢረንን የአቶም ዕቅድ ለመግታት ቆርጠው መነሳታቸው የሚታወቅ ነው። ቴህራን አቶም ቦምብ በመስራት ትጠረጠራለች።

ግብጽና የሙባራክ ውግደት

ግብጽ ውስጥ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባራክ ከሥልጣን የተወገዱበት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ተቃዋሚዎች ባደረጉት ጠቅላይ የስራ ማቆም ዓድማና የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪ ተጀመረ።  ከሰላሣ የሚበልጡት የተቃውሞው ወገን ቡድኖች በዚሁ ዕርምጃ ወታደረዊው አገዛዝ ሥልጣኑን ለሲቪል መንግሥት እንዲያስረክብ ግፊታቸውን ለማጠናከር ያስባሉ።  በሌላ በኩል የጠቅላላ ዓድማው ጥሪ በአገሪቱ ሙስሊምና ክርስቲያን ኦርቶዶክስ ምዕመናን ተኮንኗል።  በአዲሱ የግብጽ ፓርላማ ውስጥ የብዙሃን ድምጽ ያለው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ በበኩሉ እንዳስታወቀው የአገሪቱን ኤኮኖሚ በሚጎዳ በማንኛውም የዓድማ ዕርምጃ ለመሳተፍ ዝግጁ አይደለም። ወታደራዊው አመራርም በፊናው ከተመደበው ጊዜ ቀድሞ ሥልጣን ለሲቪል መንግሥት እንደማያስረክብ እንደገና አስገንዝቧል። የአገሪቱ ጦር ሃይል ባለፉት ቀናት ወታደሮቹንና የጦር ተሽከርካሪዎቹን በመላው ግብጽ  በአደባባይ በማስለፍ ጥንካሬ ሲያሳይ ነው የሰነበተው።

ኬንያ አል-ሻባብን አዳከምኩ አለች

የኬንያ መንግሥት ጦር በደቡባዊው ሶማሊያ ለአራት ውራት ባካሄደው የጥቃት ዘመቻ ከአል-ቃኢዳ ትስስር እንዳለው የሚነገርለትን እሥላማዊ የዓመጽ ቡድን አል-ሻባብን ማዳከሙንና የገንዘብ ምንጩን ማሰናከሉንም አስታወቀ። የጦሩ የመረጃና የተግባር አቀናባሪ ኮሎኔል ሣይረስ ኦጉና ለፈረንሣይ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የኬንያ የአየርና የምድር ጥቃት የአል-ሻባብን የንግድ መስመር ሲያሰናክልና ተዋጊዎቹ ቁልፍ ከሆኑ ከተሞች እንዲወጡ ሲያስገድድ 75 በመቶ የሚሆን ገቢያቸውን እንዲያጡም አድርጓል። ተያይዞ እንደተጠቀሰው በሣምንቱ የጥቃት ዘመቻ ብዙ የሻባብ የጦር መሪዎችም ሳይገደሉ አልቀሩም። ኬንያ ባለፈው ጥቅምት ወር ጦሯን ወደ ሶማሊያ ያስገባችው አል-ሻባብ ድንበር እያቋረጠ የሚያደርሰውን ጥቃትና  የውጭ ዜጎችን በማገት የሚወስደውን ዕርምጃ ለመበቀል ነበር። አል-ሻባብም በፊናው በሁለቱ ሃገራት ድንበር አኳያ ጥቃት በማድረስ በርካታ ሰዎችን ገድሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮችም በወቅቱ በምዕራባዊው ሶማሊያ መስፈራቸው የሚታወቅ ነው።

ሱ-ቺ የምርጡኝ ቅስቀሣ ጀመሩ

የበርማ የተቃውሞ ወገን መሪ አውንግ-ሣን-ሱ-ቺ ከራንጉን በስተደቡብ በምትገኘው ካውሙ በተሰኘች አውራጃ የምረጡኝ ቅስቀሣቸውን ጀመሩ። ሱ-ቺ በፊታችን መጋቢት 23 ቀን ተከታይ የፓርላማ ምርጫ መቀመጫ ለማግኘት በከፈቱት ዘመቻ በበዙ ሺህ በሚቆጠሩ የብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ሊጋ ፓርቲያቸውን መለያ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ በአደባባይ በተሰለፉ ደጋፊዎቻቸው ፊት ንግግር አሰምተዋል። ባለፈው ምርጫ  የሱ-ቺ ፓርቲ በእገዳ ምክንያት አልተሳተፈም ነበር። ታዛቢዎች እንደሚናገሩት ለ 48 ቀሪ መቀመጫዎች የሚካሄደው ምርጫ ከግማሽ ምዕት-ዓመት ወታደራዊ አገዛዝ በኋላ አገሪቱን ለመክፈት ቃል የገባው አዲሱ መንግሥት የሚፈተሽበት ነው። MM/DW/AFP